Isaiah 16

1ከምድረ በዳው ማዶ ካለችው ከሴላ፣
ለምድሪቱ ገዥ፣
ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ
የበግ ጠቦት ግብር ላኩ።
2ከጐጇቸው ተባርረው
ግራ እንደ ተጋቡ ወፎች፣
የሞዓብ ሴቶችም
በአርኖን ወንዝ መሻገሪያ እንዲሁ ይሆናሉ።

3“ምክር ለግሱን፤
ውሳኔ ስጡን፤
በቀትር ጥላችሁን
እንደ ሌሊት አጥሉብን፤
የሸሹትን ደብቁ፤
ስደተኞችን አሳልፋችሁ አትስጡ።
4የሞዓባውያን ስደተኞች ከእናንተ ጋር ይቈዩ፤
እናንተም ከአጥፊው መጠጊያ ሁኗቸው።”

የጨቋኙ ፍጻሜ ይመጣል፤
ጥፋቱ ያከትማል፤
እብሪተኛም ከምድር ገጽ ይጠፋል።
5ዙፋን በፍቅር ይመሠረታል፤
ከዳዊት ቤት
ዕብራይስጡ ድንኳን ይላል።
የሆነ፣
በፍርድ ፍትሕን የሚሻ፣
ጽድቅንም የሚያፋጥን፣
አንድ ሰው በታማኝነት በላዩ ይቀመጣል።
6የሞዓብን መዘባነን፣
እጅግ መታበዩንና ኵራቱን፣
እብሪቱንና ስድነቱን ሰምተናል፤
ትምክሕቱ ግን ከንቱ ነው።
7ስለዚህ ሞዓባውያን ዋይ ይላሉ፤
በአንድነትም ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማሉ፤
ስለ ቂርሐራሴት ከተማ ሰዎች ትዝታ፣
በሐዘን ያለቅሳሉ።
8የሐሴቦን ዕርሻ፣
የሴባማም የወይን ተክል ጠውልጓል፤
የአሕዛብ ገዦች፣
ኢያዜርን ዐልፈው፣
ምድረ በዳውን ዘልቀው፣
ሥሮቻቸውን እስከ ባሕር ሰድደው የነበሩትን
የተመረጡ የወይን ተክሎችን
ረጋግጠዋል።
9ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ተክል፣
ኢያዜር እንዳለቀሰች፣ እኔም አለቅሳለሁ፤
ሐሴቦን ሆይ፤ ኤልያሊ ሆይ፤
በእንባዬ አርስሻለሁ፤
ፍሬ ባፈራሽበት ወቅት የነበረው ሆታ፣
መከርሽም ሲደርስ የነበረው ደስታ ተቋርጧልና።
10ደስታና ሐሤትም ከአትክልቱ ቦታ ተወግዷል፤
በወይን ተክልም ቦታ ዝማሬ የለም፤
እልልታም ቀርቷል።
በወይን መጭመቂያ ቦታ የሚረግጥ የለም፤
የረጋጮችን ሆታ አጥፍቻለሁና።
11ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ እንደ በገና የሐዘን እንጕርጕሮ ታሰማለች፤
አንጀቴም ስለ ቄርሔሬስ ታለቅሳለች፤
12ሞዓብ ወደ ኰረብታዋ ብትወጣ፣
ትርፏ ድካም ብቻ ነው፤
ለጸሎት ወደ መቅደሷ ብትገባም፣
ዋጋ የለውም።
13 እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ሞዓብ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 14አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የተቀጠረ ሠራተኛ ቀን እንደሚቈጥር፣ የሞዓብ ክብርና የሕዝቧ ብዛት በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚቀረውም ሕዝብ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።”

Copyright information for AmhNASV